አጭር ትምህርተ ክርስቲያን
ከአባ ገብረሚካኤል መኮንን
በ ፲፱፻፸፪ዓ.ም ታተመ
ጥ- ማን ፈጠረን?
መ- እግዚአብሔር።
ጥ- ለምን ፈጠረን?
መ- እንድናውቀው፣ እንድንወደው፣ ትዕዛዙን እንድንፈጽም ይህንንም አድርገን መንግስተ ሰማይ እንድንገባ ፈጠረን፡፡
ጥ- እግዚአብሔር ማለት ምን ማለት ነው
መ- ፍጹም፣ረቂቅ፣ ለዘለዓለም የሚኖር ሰማይና ምድርን የፈጠረ የሁሉ ጌታ ማለት ነው፡
ጥ- እግዚአብሔር ስንት ነው?
መ- አንድ ነው።
ጥ- ወዴት ይኖራል?
መ- በሁሉ ስፍራ ይኖራል፡፡
ምስጢረ ሥላሴ
ጥ- ምስጢረ ሥላሴ ምን ማለት ነው
መ- በአንድ አምላክ ሦስት አካላት አብ፣ ወልድ፣ መንፈስ ቅዱስ አሉ ማለት ነው፡፡
ጥ- አብ አምላክ ነውን?.
መ- አዎን
ጥ- ወልድ አምላክ ነውን?
መ- አዎን
ጥ- መንፈስ ቅዱስ አምላክ ነውን?
መ- አዎን
ጥ- እንዲህ ከሆነ ሦስት አምላክ ናቸውን?
መ- አይደሉም አንድ አምላክ ብቻ ናቸው፡፡
ጥ- ሦስት አካላት አንድ አምላክ ብቻ መሆናቸው በምን ይታወቃል ?
መ- መለኮታቸው አንድ ስለ ሆነ አንድ አምላክ ብቻ መሆናቸው ይታወቃል፡፡
ምስጢረ ሥጋዌ
ጥ- ምስጢረ ሥጋዌ ምን ማለት ነው?
መ- ወልደ እግዚአብሔር ሰው ሆነ ማለት ነው፡፡
ጥ- ከማን ሰው ሆነ
መ- ከእግዝእትነ ማርያም ሰው ሆነ
ጥ- በማን ሥራ
መ- በመንፈስ ቅዱስ ሥራ
ጥ- የመንፈስ ቅዱስ ሥራ ምን ማለት ነው
መ- እመቤታችን በድንግልናዋ መጸነስ፣ በድንግልናዋ መውለድ ማለት ነው፡፡
ጥ- ወልደ እግዚአብሔር ከእመቤታችን በተወለደ ጊዜ ስሙ ማን ተባለ?
መ- ኢየሱስ ክርስቶስ ተባለ፡፡
ጥ- ኢየሱስ ክርስቶስ ምንድን ነው?
መ- ፍጹም አምላክ ፍጹም ሰው ነው፡፡
ጥ- በኢየሱስ ክርስቶስ ስንት አካል አለ?
መ- አንድ ብቻ የወልደ እግዚአብሔር አካል አለ፡፡
ጥ- ወልደ እግዚአግሔር ለምን ሰው ሆነ?
መ- እኛን ለማዳን ሰው ሆነ
ጥ- እንዴት አድርጎ አዳነን?
መ- በመስቀል ተሰቅሎ ደሙን አፍሶ ሞቶ አደሰነን፡፡
የሰው ፍጻሜዎች
ጥ- የሰው ፍጻሜዎች ስንት ናቸው?
መ- አራት ናቸው እነዚህም ሞት፣ ፍርድ፣ ገሃነመ እሳት፣ መንግስተ ሰማይ ናቸው፡፡
ጥ- ሞት ምን ማለት ነው
መ- የነፍስና የሥጋ መለያየት ማለት ነው
ጥ- ከሞት በኋላ ነፍስ ምን ትሆናለች?
መ- ፍርድ ልትፈረድ በእግዚአብሔር ፊት ትቆማለች፡፡
ጥ- ከዚያ በኋላ ወዴት ትሄዳለች?
መ- ደግ የሠራች ወደ መንግሥተ ሰማይ ትሄዳለች ክፉ የሠራች ወደ ገሃነመ እሳት ትወርዳለች፡፡
ጥ- ዓለም ሲያልቅ ምን ይሆናል?
መ- የሞተ ሰው ሁሉ ከመቃብር ይነሳል፡፡ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ፍርድ ሲፈርድ ከሰማይ ወደ ምድር ይመጣል፡፡
ኀጢአት
ጥ- ኀጢአት ምን ማለት ነው?
መ- የእግዚአብሔር ሕግ አውቆ ማፍረስ ማለት ነው፡፡
ጥ- ስንት ዓይነት ኀጢአት አለ ?
መ- ያባታችን የአዳም ኀጢአት ተብሎ ሁለት ዓይነት ኀጢአት አለ፡፡
ጥ- ያባታችን የአዳም ኀጢአት በሁላችን ደርሷልን?
መ- ከእመቤታችን በቀር አዎን በሁላችን ደርሷል፡፡
ጥ- ምን ያደርገናል?
መ- ወደ መንግሥተ ሰማይ እንዳንገባ ይከለክለናል፡፡
ጥ- በምን ይጠፋል?
መ- በምስጢረ ጥምቀት ይጠፋል፡፡
ጥ- የራሳችን ኀጢአት በስንት ይከፈላል?
መ- ታላቅና ታናሽ ተብሎ በሁለት ይከፈላል፡፡
ጥ- ታላቅ ኀጢአት ምን ያደርገናል?
መ- የእግዚአብሔር ጠላቶች የሰይጣን ባሮች ያደርገናል ወደ ገሃነመ እሳት ያወርደናል፡፡
ጥ- ታናሽ ኀጢአት ምን ያደርገናል?
መ- የእግዚአብሔር አሳዛኞች ያደርገናል ወደ ንሳሓ ቦታ ያወርደናል፡፡
ጥ- የኛ ኀጢአት ትልቁም ትንሹም በምን ይጠፋል?
መ- በምስጢረ ንስሓ ይጠፋል፡፡
ቤተ ክርስቲያን
ጥ- ቤተክርስቲያን ምን ማለት ነው?
መ- የተጠመቁ ለጌታችንና ለምስለኔው የሚታዘዙ ከርሱ ጋር በሃይማኖት በምስጢራት በሕግም አንድ ሁነው የሚኖሩ የሰው ማኀበር ማለት ነው፡፡
ጥ- ቤተክርስቲያንን የተከለ ማነው?
መ- ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ነው፡፡
ጥ- የቤተክርስቲያን አለቃ ማነው?
መ- ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በሐዋርያት ላይ አለቃ የሾመው ቅዱስ ጴጥሮስ ነው ከርሱም ቀጥሎ በሮማ የተቀመጡ ሊቃነ ጳጳሳት የቤተክርስቲያን አለቆች ናቸው፡፡
ጥ- እውነተኛይቱ ቤተክርስቲያን የምትታወቅባቸው ምልክቶች ስንት ናቸው?
መ- በጸሎተሃይማኖት ቤተክርስቲያን አንዲት ቅድስት ካቶሊካቂት ሐዋርያዊት ናት ተብሎ እንደተነገረ አራት ምልክቶች አሉ፡፡
ጥ- እነዚህ ምልክቶች የት ይገኛሉ?
መ- በካቶሊካዊት ቤተ ክረስቲያን ብቻ ይገኛሉ፡፡
ዐሠርቱ ቃላት(የእግዚአብሔር ትእዛዝ )
ጥ- የእግዚአብሔር ትእዛዛት ስንት ናቸው?
መ- ዐሥር ናቸው እነዚህም
፩ ከኔ በቀር ሌላ አምላክ የለህም
፪ የእግዚአብሔርን ስም በከንቱ አትጥራ
፫ ዕለተ ሰንበትን አክብር
፬ አባት እናትህን አክብር
፭ አትግደል
፮ አታመንዝር
፯ አትስረቅ
፰ በሐሰት አትመስክር ጉል
፱ የሰውን ሚስት አትመኝ ተብሎ
፲ የሰውን ገንዘብ አትመኝ ናቸው፡፡
የቤተክርስቲያን ትእዛዝ
ጥ- የቤተክርስቲያን ትእዛዛት እነማናቸው?
መ- ቀጥለው የሚገኙት ናቸው፡፡
፩ በእሑድ ቀን በበዓል ቀን ቅዳሴን ስማ
፪ ቤተክርስቲያን ያዘዘችውን ጾም ጹም
፫ በዓመት ቢያንስ አንድ ጊዜ ተናዘዝ
፬ በፋሲካ ወራት ቁረብ
፭ ካሥር ለቤተክርስቲያን አንድ ስጥ
የቤተክርስቲያን ምሥጢራት
ጥ- የቤተክርስቲያን ምሥጢራት ምን ማለት ነው
መ- ሰው እንዲጸድቅ ጸጋ የሚሰጡ ምልክቶች ማለት ነው፡፡
ጥ- የቤተ ክርስቲያን ምሥጢራት ስንት ናቸው?
መ- ሰባት ናቸው
፩ ጥምቀት
፪ ሜሮን
፫ ቁርባን
፬ ንስሓ
፭ መጽሐፈ ቀንዲል
፮ ክህነት
፯ መጽሐፈ ተክሊል ናቸው፡፡
ጥ- ጥምቀት ምን ማለት ነው?
መ- የአዳምን ሐጢያት የሚያጠፋ ሰውን ክርስቲያንና የእግዚአብሔር ልጅ የሚያደርግ መንግስተ ሰማይን የሚያወርስ ምስጢር ማለት ነው፡፡
ጥ- ጥምቀት የግድ ያስፈልጋልን?
መ- ያለጥምቀት ደኅንነትና መንግሥተ ሰማይ አይገኝምና አዎን የግድ ያስፈልጋል፡፡
ጥ- ሜሮን ምን ማለት ነው?
መ- ክርስቲያንን የሚያጠና መንፈስ ቅዱስን የሚሰጥ ምስጢር ማለት ነው፡፡
ጥ- ቁርባን ምን ማለት ነው?
መ- በኅብስትና በወይን መልክ በውነት የጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሥጋን ደምን ነፍስን መለኮትንም የያዘ ምስጢር ማለት ነው፡፡
ጥ- የቁርባን ምስጢር በምን ሥርዐት ይደረጋል?
መ- በቅዳሴ ሥረዐት ይደረጋል፡፡
ጥ- መቼ የግድ መቁረብ ይገባል?
መ- በፋሲካ ወራትና በሞት ጊዜ የግድ መቁረብ ይገባል፡፡
ጥ- እንዴት ሆኖ መቁረብ ይገባል?
መ- ትልልቁን ኀጢአት በንስሓ አጥፍቶ ከእኩለ ሌሊት እስከ ቁርባን ጊዜ ጾም ጾሞ መቁረብ ይገባል፡፡
ጥ- ንስሓ ምን ማለት ነው?
መ- ከጥምቀት በኋላ የተሰራውን ኀጢአት የሚያጠፋ ሚስጢር ነው ።
ጥ- ንስሓን በሚገባ ለማድረግ ምን ያስፈልጋል?
መ- ንስሓን በሚገባ ለማድረግ ፩ የሠሩትን ኀጢአት ማሰብ ፪ በርሱ ማዘን ፫ ወደ እርሱ እንዳይመለሱ ቁርጥ ፈቃድ ማድረግ ፬ ያሰቡትን ኀጢአት ለነፍስ አባት መናዘዝ ፭ የነፍስ አባት የሰጠውን ቀኖና በሙሉ መፈጸም ያስፈልጋል፡፡
ጥ- መጽሐፈ ቀንዲል ምን ማለት ነው?
መ- በብርቱ ታሞ ሞት ለሚያስፈራው ሰው ለነፍሱና ለሥጋው የሚጠቅም ምስጢር ነው፡፡
ጥ- ክህነት ምን ማለት ነው?
መ- ካህናትን የሚቀድስ የቤት ክርስቲንንም ምስጢራት ለመፈጸም ሥልጣን የሚሰጣቸው ምስጢር ማለት ነው፡፡
ጥ- መጽሐፈ ተክሊል ምን ማለት ነው?
መ- ባልና ሚስት እስከ ሞታቸው ጊዜ ድረስ አንድነት የሚኖሩበትን ልጆቻቸውንም በቤተክርስቲያን ሥርዓት የሚያሳድጉበትን ጸጋ የሚያገኙበት ምሥጢር ነው፡፡
ጸሎት
ጥ- ጸሎት ምን ማለት ነው፡፡
መ- እግዚአብሔርን ለማመስገንና ለመለመን ነፍሳችንን ወደ እግዚአብሔር ማሳረግ ማለት ነው።
ጥ- ጸሎት የግድ ያስፈልጋልን?
መ- ያለጸሎት ጸጋ አለጸጋም ደኅንነት አይገኝምና አዎን የግድ ያስፈልጋል ።
ጥ- ጸጋ ምን ማለት ነው?
መ- እንድንድን እግዚአብሔር የሚሰጠን ረድኤት ነው፡፡
ጥ- ጸሎት መቼ ማድረግ ያሰፈልጋል?
መ- ጠዋትና ማታ በፈተናም ጊዜ ሥራችንንም ወደ እግዚአብሔር ለማቅረብ ብዙ ጊዜ ጸሎት ማድረግ ያስፈልጋል፡፡
ጥ- ከሁሉም የሚበልጡ ጸሎቶች እነማናቸው?
መ- ቅዳሴ አቡነ ዘበሰማያት ሰላም ገብርኤል . ጸሎተሃይማኖት ናቸው፡፡
ጥ- ለማን ጾሎት ማድረግ ያስፈልጋል?
መ- ለራሳችን ለዘመዶቻችን በጎ ሥራ ለሠሩልን ለሰው ሁሉም ማድረግ ያስፈልጋል፡፡
በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን
አምላኬ ሆይ እሰግድልሃለሁ በልቤም እወድሃለሁ ስለፈጠርከኝና ክርስቲያን ስላደረከኝ በዚች ለሊትም (በዚህች ቀንም) ስለጠበከኝ አመሰግንሃለሁ፡፡
ሥራዬን ሁሉ ላንተ አቀርባለሁ ከኃጢአት እንድትጠብቀኝ ከክፉ ነገርም ሁሉ እንድታድነኝ እለምንሃለሁ፡፡
አባታችን
በሰማይ የምትኖር አባታችን ሆይ ስምህ
ይመስገን መንግሥትህ ይምጣ ፈቃድህ
በሰማይ እንደሆነ እንዲሁ በምድር ይሁን
የዕለት እንጀራችንን ዛሬ ስጠን እኛ
የበደሉንን ይቅር እንደምንል በደላችንን
ይቅር በለን ከክፉ ሁሉ ሰውረን እንጂ ወደ
ፈተና አታግባን መንግሥት ኃይልና ክብር
ለዘለዓለም ነውና፡፡ አሜን፡፡
ሰላም
ጸጋ የመላሽ ማርያም ሆይ ሰላም ላንቺ ይሁን
እግዚአብሔር ካንቺ ጋር ነው፤ ከሴቶች ሁሉ
የተባረክሽ ነሽ የሆድሽም ፍሬ ኢየሱስ
ክርስቶስ የተባረከ ነው፡፡ ቅድስት ማርያም
የአምላክ እናት ለኛ ለኃጢአተኞች አሁንም
በሞታችንም ጊዜ ለምኝልን፡፡
ምስጋና
ለአብና ለወልድ ለመንፈስ ቅዲስ ምስጋና ይሁን፡፡ አሁንም ዘወትር ለዘለዓለምም አሜን፡፡
የሐዋርያት ጸሎት ሃይማኖት
ሁሉን በሚችል ሰማይንና ምድርን በፈጠረ በእግዚአብሔር አብ አምናለሁ፤
የአብ አንድ ልጅ በሆነው በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስም አምናለሁ፤
እሱ በመንፈስ ቅዱስ ተፀነሰ፤
ከድንግል ማርያም ተወለደ በጴንጤናዊው ጲላጦስ ዘመን ተሰቃየ ተሰቀለ፤
ሞተ ተቀበረ ወደ ሲኦል ወረደ በሦስተኛው ቀን ከሞት ተነሣ፤
ወደ ሰማይ ዓረገ ሁሉን በሚችል በእግዚአብሔር አብ ቀኝ ተቀመጠ ያሉትንና የሞቱትን ሊፈርድ ዳግመኛ ይመጣል፤
በመንፈስ ቅዱስ አምናለሁ፡፡ የሁሉም በሆነችው በቅድስት ቤተክርስቲያን በቅዱሳንም አንድነት አምናለሁ፡፡
በኃጢአት ሥርየት በሙታን ትንሳኤ በዘለዓለም ሕይወት አምናለሁ፡፡ አሜን
የሃይማኖት ሥራ
አምላኬ ሆይ አንተ የገለጥከውን ቅድስት ቤተክርስቲያን የምታምነውንና የምታስተምረውን ሁሉ አምናለሁ፡፡
የተስፋ ሥራ
አምላኬ ሆይ ተስፋ የሰጠኸው ቃልህ እውነተኛ ነውና ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ ትሩፋት የዘለዓለምን ሕይወት እንድትሰጠኝና ወደዚያውም ለመድረስ ጸጋህን እንደምታድለኝ ተስፋ አደርጋለሁ፡፡
የፍቅር ሥራ
አምላኬ ሆይ አለመጠን ደግ አለመጠን ተወዳጅ ነህና እወድሃለሁ፡፡ ስላንተ ፍቅር ሰውን ሁሉ እወዳለሁ፡፡
የንስሐ ሥራ
አምላኬ ሆይ ፍጹም ተወዳጅ ነህ ኃጢአትን የምትጠላ ነህ በኃጢዘቴ ስለበደልሁህ እጅግ አዝናለሁ ማረኝ ዳግመኛ ወደ ኃጢአት አልመለስም በጸጋህ ከኃጢአት ምክንያት ሁሉ አርቃለሁ፡፡
የኑዛዜ ጸሎት
ሁሉን ለሚችል ለእግዚአብሔር ኃጠአቴን እናዘዛለሁ፡፡ በማሰብ በመናገር በማድረግ ተግባሬን ባለመፈጸም በጣም በድያለሁና ስለዚህ ወደ እግዚአብሔር አምላካችን እንዲጸልዩልኝ ቅድስት ድንግል ማርያምን መላእክትን ጻድቃን ሁሉ እለምናለሁ፡፡
ወደ ቅድስት ቤተሰብ ጸሎት
ኢየሱስ ማርያም ዮሴፍ ልቤን ነፍሴን ሕይወቴን እሰጣችኋለሁ፡፡ ኢየሱስ ማርያም ዮሴፍ በሞት ጊዜ እርዱኝ ኢየሱስ ማርያም ዮሴፍ በእጃችሁ በሰላም አሳርፍኝ፡፡
በኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን
ሐዋርያዊ ሥራ መምሪያ የተዘጋጀ
አዲስ አበባ