1. ሰላም መሪ ኮከብ
1
ሰላም መሪ ኮከብ
ቅድስት ያምላክ እናት
ዘለዓለም ድንግል
ለኛ ሰማይ ደጅ።
2
ሰላም ስትቀበይ
ከገብርኤል ልሳን
በሰላም አኑሪን
የሔዋንን ክፈይ ።
3
የታሰረ ፍቺ
ዕዉራንን አብሪ
ጭንቃችንን አንሺ
መልካምን ሁሉ አምጪ ።
4
እናታችን ሁኚ
ጸሎትን አቅርቢ
ለተወለደልን
ያንቺም ልጅ ለሆነ ።
5
የደናግል ድንግል
ከሁሉ ማሪ ነሽ
ከክፋት ሰውሪን
ገር ልብ ጥሩም አርጊን።
6
ጥሩነትን ስጪን
መንገድን አቅኚ
የሱስን አይተን
ዘወትር ደስ እንዲለን ።
7
ለአብ ወዳሴ ይሁን
ለክርስቶስም ክብር
ለመንፈስ ቅዱስም
ባንድነት ለሦስቱም።
አሜን
2. ኢየሱስ አትርሳን
ኢየሱስ አትርሳን
ለቅሷችንን አድምጠን
ከጥፋት አድነን
ና ድረስልን ።
1
ገሥግሠኽ ድረስልን
ነፍሳችንን ልታድን
ልንሞት ነው አድነን
ኢየሱስ አትርሳን
ለቅሷችንን ስማልን
ከጥፋት ሰውረን
ና ድረስልን ።
2
መሓሪ አምላክ ታደገን
በንስሓ ጐስቍለን
ካንተ በቀር ተስፋ አጣን
ዲያብሎስ ሊፈጀን
ገሠገሠ ሊያጠፋን
አይተኽ ጭንቃችንን
ና ድረስልን ።
3
ምስጉን አምላክ ባይናችን
አንተን ማየት ተመኘን
ድረስ ቶሎ ቅረበን
ዘመኑ በዛብን
ዘገየብን መምጫኽ ቀን
አስበኽ ወገንኽን
ና ድረስልን ።
4
አምላካችን በፍርድ ቀን
ባሮችኽን ደስ አሰኘን
በቀኝኽም አስቀምጠን
ጠብቀን ትዛዝኽን
እንዳይጠፋ ዋጋችን
በምንሞትበት ቀን
ና ድረስልን ።
5
ባለም ያሉ ፍጡራን
ያላወቁ መምጣትኽን
እንዳይቀሩ በሐዘን
አትናቅ ሥራኽን
አብራላቸው ብርሃንኽን
አንድ መንጋ እንዲሆን
ና ድረስልን።
3. ልደት ቤተ- ልሔም ዛሬ ሌሊት
1
ቤተ ልሔም ዛሬ ሌሊት
ተደንቃለች በታምራት
አምላክ ወሰብእ ተወልዶላት
ተከባለች በመላእክት ።
2
እረኞች ሆይ ንገሩን
የዛሬን በዓል ክብሩን
ብንሰማ ዜማችሁን
መጣን እንደናንት ደስ ብሎን ።
3
የእስራኤል ንጉሥ የዳዊት
ተወልዷል በዚች ሌሊት
የገብርኤልም ብሥራት
ተፈጸመ ዛሬ በውነት ።
4
ያዳም ልጆች ነቃ በሉ
የመልአኩን ቃል ተቀበሉ
ሰላማችን መጣ እልል በሉ
ሊያድነን ነው ከሃጢኣት ሁሉ።
5
ኢየሱስ ሆይ የዳዊት ልጅ
ታደገን ከዲያብሎስ እጅ
ክፈትልን የሰማይን ደጅ
አውጣን ስበኽ ከሲኦል ደጅ ።
4. ወልድ አምላክ ተወለደልን
ወልድ አምላክ ተወለደልን
በእንቢልታና ባማረ ዜማ
ወልድ አምላክ ተወለደልን
ደስ ይበለን ምክሩን እንስማ
1
ካራት ሺ ዓመት በለጠ
ነቢያቶች ይመጣል ካሉ
ካራት ሺ ዓመት በለጠ
ሲጠብቀው ሕዝቡ ሁሉ ።
2
እንዴት መልካም እንዴት ውብ ነው
በውነት ፊቱ ያምላክ መልክ ነው
እንዴት መልካም እንዴት ውብ ነው
ሰላማችን እርሱ ነው ።
3
እበረት ሆነ ማደሪያው
ጉዝጓዙም ሣር ገለባ ነው
እበረት ሆነ ማደሪያው
የሰውን ውርደት ወደደው።
4
በውነት ያምላካችን ልጅ ነው
ገነትም የርሱ ሕይወት ነው
በውነት ያምላካችን ልጅ ነው
ስለኛ የደኸየው ነው ።
5
ኢየሱስ ክብርኽን ናቅኽ
ውርደትን ስለኛ ፈቀድኽ
ኢየሱስ ክብርኽን ናቅኽ
የሰውንም ኵራት ጠላኽ ።
6
አማኑኤል ቢወለድልን
አምላካችን ይቅር አለን
አማኑኤል ቢወለድልን
ሌት ኼደ ብርሃን ነጋልን ።
7
ኢየሱስ ሆይ ንጉሣችን
መድኃኒት ነህ ለነፍሳችን
ኢየሱስ ሆይ ንጉሣችን
አስታረቅኸን ካምላካችን።
5. ሰላም ቤተ ልሔም
ሰላም ቤተ ልሔም
ጌታ ባንቺ ቢያርፍ
ሰላም ለማርያም
ሰላም ለዮሴፍ ።
1
እንደ ከብት እረኛ
እበረት ነበርን
ከሰማያት መጥቶ
መልአክ ሲታየን ።
2
ዓለም በመላዋ
ደስ ደስ ይበልሽ
ቀድሞ እምትመኚው
እነሆ ተስፋሽ ።
3
በሰማይ ይመስገን
በምድርም በሰው አፍ
ሊያድን መጥቷልና
ሰውን ከሞት አፋፍ ።
4
እንደ መላእክቱ
እኛ እናመስግን
ወደ ቤተ · ልሔም
በቶሎ ቀርበን ።
5
ያምላክ ልጅ ሕፃኑ
ከበረት ነወይ
እናቱ ታቅፋው
አባቱ እሰማይ ።
6
ቅድስት ማርያም
ከበረት ያዘንሺ
አሕዛብን መልሺ
አንቺን ይውደዱሺ ።
7
ቅዱስ መልአክ ሆይ
ከኢየሱስ ፍቅር ጋር
በብርቱ አቈራኘን
በኋላ እንዳንቀር ።
8
አሕዛቦች ሁሉ
ያልታዘዛችሁ
ኢየሱስን · ወደዱ
እሱን አምናችሁ ።
6. በላይኛው ሰማይ
በላይኛው ሰማይ
ክበር አምላካችን
ደግሞም በምድርም ላይ
ሰላም ለሁላችን ።
1
እግዚአብሔር ቢወደን
ሰላምን ላከልን
ከጥፋት አዳነን
ልጆቹ አደረገን ።
2
ምን ያህል ደስታ ነው
በእግዚአብሔር አጠገብ
ምን ያህል እልልታ ነው
በምድር ላይ ለኣሕዛብ ።
3
ላለም ሁሉ ክርስቲያኖች
ዛሬ ደስታ ነው
እንደ መላእክቶች
ዜማው የልልታ ነው ።
4
ምነው ሰላማችን
በበረት ተወለደ
እንዴት አምላካችን
እኛኑ ወደደ።
5
ዓለምን ለማዳን
አዋረደ ራሱን
ገነትን ሊከፍትልን
ወደደ መስቀልን ።
6
ፍጡር አረመኔዉም
ለክርስቶስ ይስገድ
በውነት እርሱነውሰላም፣
የለም ሌላ መንገድ ።
7. ግሩም ሕፃን ኢየሱስ ክብር
ግሩም ሕፃን ኢየሱስ ክብር
ለቅዱሳን ነዲድ ፍቅር
አቃጥለን በፍቅርኽ
ያለኸን አንተ ነኽ
ፍጹም ፍቅር ነኽ ።
1
ፍቅሩ ኢየሱስ ብሎ ጠራው
የጻድቃኖች መዝገብ ነው
እንግዴህ እንስማው
እንከተለው
ፍጹም ፍቅር ነው ።
2
ሰማይ እርሱን ያደንቀዋል
መላእክትም ይሰግዱታል
በውነት እርሱ አምላክ ነው
እኛም እናክብረው
ፍጹም ፍቅር ነው።
3
እንደ ድኃ ተወለደ
መከራንም ወደደ
በውነት እርሱ ቻይ ነው
የሚያስደንቅም ነው
ፍጹም ፍቅር ነው
4
እርሱ መድኃኒታችን ነው
ለኀጥኣን ተስፋ ነው
ፍቅሩ ልክ የለው
የጻድቃን ወዳጅ ነው
ፍጹም ፍቅር ነው ።
5
እላንት የእግዚአብሔር መላእክት
የኛን ፍቅር አበርቱልን
እንድንወደው እርሱን
አንዳችንም እንዳንተወው
ፍጹም ፍቅር ነው
6
ክበር ኢየሱስ በኛ መኻል
ብርሃናችን ሆነኻል
አንተን ጠርተንኻል
ያለኸን አንተ ነኽ
ፍጹም ፍቅር ነው
8. ሆሣዕና ስንል
ሆሣዕና ስንል
ጌታችን ኢየሱስ
እኛ ውስጥ እደር
እኛንም አድስ ።
1
ሆሣዕና ስንል
ጌታችን ኢየሱስ
አምላክና ሰው
ባንድ አካል ነው ።
2
ሆሣዕና ስንል
ጌታችን ኢየሱስ
ስግደቱ አንድ ነው
ላምላክ ለሰው ።
3
ሆሣዕና ስንል
ጌታችን ኢየሱስ
እኛን ሊያድነን
ሰው ሆነልን ።
4
እንዴት ላንተ ይብቃ
የኛ አባት ጭቃ
5
ሰው ሆነልን
እንዴት ወዶን ።
6
የኛ አምላክ ነኽ
ምስጋና ይግባኽ ።
7
ብትመጣልን
ከጥፋት ዳንን ።
8
የሰይጣን ተስፋ
ፈጽሞ ጠፋ ።
9
ምሕረትን አምጣ
ጤና ስናጣ
10
ራብ ሲሆን
ምግብ ስጠን ።
11
በጭንቁ ጊዜ
አውጣን ያነዜ ።
12
ለቤትኽ ሰው
ደጉን ምራው ።
13
በጃችን ሥራ
በረከትን ዝራ ።
14
በፍርድኽ ቀን
ይቅር በለን።
9. የኢየሱስ ልብ
ላንተ ይሁን ላንተ ይሁን› ልቤ ላንተ ይሁን
ላንተ ይሁን ላንተ ይሁን ልቤ ላንተ ይሁን።
1
ልቤ ላንተ ይሁን
በምሥጢረ ቍርባን
የሕይወቴ መድን
አንተ ብቻ ሁን ።
2
ልቤ ላንተ ይሁን
ካንተ ወዲያ ጌታ
ነፍሴ የት አግኝታ
በፈጠርኸው ቦታ
3
ልቤ ላንተ ይሁን
ያንተ ነው ከጥንቱም
የፈጠርኸው ቀድሞም
ያዳንኸው ኋላም ።
4
ልቤ ላንተ ይሁን
ሥጋኽን አብልተኽ
ደምኽን አጠጥተኽ
ተድላ አኑረኽ ።
5
ልቤ ላንተ ይሁን
ላለፈው ማረኝ
ዓለምስ አይሻኝ
ምንም ቢያደርገኝ ።
6
ልቤ ላንተ ይሁን
ዓለምን ከመግዛት
ላንተ ባርነት
ይበልጣል በውነት ።
7
ልቤ ላንተ ይሁን
ከቶ እንዳረሳኽ
በምን ልጻፍኽ
ወዴት ላኑርኽ ።
8
ልቤ ላንተ ይሁን
ለዘለዓለም
ድንግል ማርያም
ታማልደኝ ፍጹም ።
10. የየሱስ ልብ የሕይወቴ ነኽ ጣም
የየሱስ ልብ የሕይወቴ ነኽ ጣም
አንተን ይውደድ ለዘላለም
ልቤ ነዶ ነዶ ነዶ ሲያቆም
ዛሬ ላንተ ላንተ ነው ኋላም ።
1
የመጣኹት እመኻከላችሁ
ቅዱስ ፍቅርን ላነድላችሁ
ምኞቴንም ደግሞ ልንገራችሁ
ያመጣኹት ሲቃጠል ባየሁ ።
2
ባወቅኽማ የፍቅሬን ስፋቱን
ልጄ ልቤን የሚያግለውን
በመጣኽ ዘኽ ምስጋናኽን
በደስታ ገንዘቤ ልትሆን ።
3
እንድወድኽ አንተ ትሻለኽ ወይ
እንድወድኽ መጣኽ ወይ ከላይ
ዋ ለኔማ ክብሬ አይደለኽም ወይ
ፍጹም ንጉሥ የምድር • የሰማይ ።
4
አንድ ምኞት ሌላም አልደባልቅ
ያንተን ፍቅር እንዳልነጠቅ
አንተን ከቶ ከቶም አለመራቅ
ብሞትም ብቆምም ብወድቅ ።
11. ኢየሱስ ሆይ ሲጠሩኽ
1
ኢየሱስ ሆይ ሲጠሩኽ
ደስታ ነኽ ሲያስቡኽ
ከማር ይልቅ በብዙኅ
ላፍ ይጥማል ትዝታኽ።
2
ካንተ ወዲያ ኢየሱስ
ምን ደግ አለ ምን ልስልስ
አይሰማም ካንተ ይብስ
ባሳብም የለ ጭርስ ።
3
ለበደሉ ተስፋ ነህ
ውብ ነህ ለሚመጡብህ
ምንኛ ቸር ነህ ለሹህ
ምን ትመስል ላገኙህ ።
4
ምላስም አይናገረው
ከቶ ፊደልም አይጽፈው
የደረሰበት ይወቀው
ያንተ ፍቅር ምን ያለነው
5
ኢየሱስ ሆይ ደስታችን
ኋላም ደግሞ ገንዘባችን
ባንተ ይሁን ክብረታችን
አሳባችን ምኞታችን ።
6
የምትደነቅ ንጉሥ
አሸናፊው ኢየሱስ ።
ይቸግራል በምላስ
ሲናገሩት ፍቅርህስ ።
7
ደስታ ነህ ለልባችን
ፍጹም ብርሃን ለውቀታችን
ካንተ ወዲያ አምላካችን
ተከተተ ምኞታችን ።
8
አፋችን አንተን ይጠራል
ምግባራችን አንተን ይላል
ልባችን አንተን ይወዳል
ካንተ ወዲያ ምን ይመኛል ።
9
ኢየሱስ የሰማይ ክብር
ስትሰማ የምታምር
ላፋችን ወለላ ማር
ለልባችንም ሱካር ።
10
ለሚቀምሱህ ትርባለህ
ለሚጠጡህ ትጠማለህ
ሌላ ፍቅር ትሰጣለህ
አንተው ብቻ ትበቃለ
12. መድኃኒት የሱስ ብቻ ነው
1
መድኃኒቴ የሱስ ብቻ ነው
ብዙ መልካም ላመነው
ልከተለው ልውደደው
በርሱ እንጂ ነው መዳኛው ።
2
የኔ የሱስ ቅኑ ጌታ
ለኔ ብሎ ተንገላታ ።
ኃይል እያለው የበረታ
ተጨነቀ ጎልጎታ ።
3
በጭንቅህ እኔ ልጨነቅ
በመከራህ ልጣበቅ
ከመስቀልህ አልራቅ
ከናትሀ ጋር ልጠብቅ ።
4
እናትህ ቆማ ያየሃት
ልቧን እሳት ሲፈጃት
የኃዘን ሴይፍ ሲወጋት
ይጨንቀኛል ሳስባት ።
5
መሓሪ ከልብህ ማረኝ
ከመከራሀ አካፍለኝ
ወዳንተ ዘንድ አቅርበኝ
በመንግሥትህ አስበኝ
6
ገመድህ እኔን ይሳበኝ
ግርፋትህ ይገረፈኝ
በችንካርህ ቸንክረኝ
ንጹሕ ደምህ ይጠበኝ
7
በመስቀል የፈሰሰው ደም
ቤዛ ሆነ ለዓለም
እኔን ያንሣኝ ከድካም
ባንቺ ልመና ማርያም ።
13. እነሆ ገሩ ልቡ
እነሆ ገሩ ልቡ
ለወደቀ ማሰቡ
የኛን ቁስል ማጠቡ
ድንቅ ጥበቡ ።
1
ጥሎኝ ወምበዴ
ቀርቶ መሔዴ
ሆነኝ ዘመዴ
ብርቱ መውደዴ ።
2
ቀድሞ ያየኝ
ሳያዝንልኝ
ልብህ ቢራራ
አነሣኸኝ ።
3
እንደ ልማድህ
እንደውቀትህ
ቀረብ አርገኝ
ልቤን ይዘህ ።
4
ገሩ አትቆጣ
ጸጋህን አምጣ
ያ የምታውቀው
ደካማህ መጣ ።
5
ብዙ አጥፍቼህ
አሳዝኜህ
ማረኝ ልልህ
መጣሁልህ ።
6
በደሌን እርሳ
ወቀሳን አታንሳ
መምጣቴ ብቻ
ይሁን ካሣ ።
14. ገሩ ልብህ ምሕረት የመላው
ገሩ ልብህ ምሕረት የመላው
በኃጢአት እኛ ስንወጋው
እምቢም አይል ማረኝ ለሚለው
ጥቂት እንኳ ትንሽ ቂም የለው
ኦ የሱስ ።
1
በክፉ አመል ስንቸነክርህ
ከአይሁድ · ጋራ ተባብረንብህ
ዳሩ ግና ምን ጊዜም ቸር ነህ
ይቅር በለን በገሩ ልብሀ
ኦ የሱስ ።
2
በቄስ ዦሮ ያቀረብነውን
የኛን ስራ ምናምንቴውን
በይቅርታ አጥፋው አሁኑን
ካለማወቅ እንደትቆጥርልን
ኦ የሱስ ።
3
በኛ በኵል ምንስ የታለና
ባንተ በኵል ምሕረት ሞልቷልና
ገሩ የሱስ አሁን በቶሎ ና
ካንተ ጋራ ፍቅር እንዲጠና
ኦ የሱስ ።
4
ንገሥ ንገሥ ያንተ መንግሥት ይስፋ
ከሰው ልጅ ዘር አንድኳ እንዳይጠፋ፣
ላለም ሁሉ አንተ ሁነን ተሥፋ
በመታመን በልብህ ደገፋ
ኦ የሱስ ።
15. ይክበር ለዘለዓለም
ክቡር ቍርባን ።
ይክበር ለዘለዓለም
ይክበር የየሱስ ቍርባን
1
ትልቅ ድንቅ አድርጎልን
ለፍቅራችንም ብሎ
ኢየሱስ ሌትና ቀን
ይቀመጣል ታስሮ ።
2
ኦ እጅግ ክቡር ቍርባን
የሰማይ ምግብ ነው
እንጀራ የመሰለን
የገነት ንጉሥ ነው ።
3
እርሱ ነው የቅዱሳን
የመላእክትም ጌታ ነው
ፍቅራችንን ስጠን
ለኛ ብሎ እዚ ነው ።
4
ሁሉ ቀን ለኃጢአታችንም
በቄሱ እጅ ይሳላል
ለሕይወታችንም
ሥጋውን ይሰጠናል
5
ኦ ክቡር ምስጢር ቁርባን
ለኛ ከሰማይ ወጣህ
ሁላችን መጣንልህ
ደስ ብሎን አመሰገን ።
6
የፍቅር ምድጃችን
በውነት ኢየሱስ ነው
ልባችንን አቀረብን
የጠራንም ቃሉ ነው
7
የምድር ላይ ያመስግነው
የማይታይ እግዜር ነው፣
በሰማይ አኢት ነው
ደስታችን እርሱ ነው ።
8
ይክበር የኢየሱስ ቍርባን
እምድር ላይ ይመስገን
እሰማይ ለዘለዓለምን
ይክበር ይመስገን ።
16. ኦ እጅግ ክቡር ቊርባን
ኦ እጅግ ክቡር ቍርባን
እግዜር የሚመግበን
አምናለሁ ደግሞም እርሱን
እርሱው ነግሯል ይሁን ።
1
ሲያስተምር ለቀሳውስጥ
እንደኔ አድርጉ በውነት
የኔ ሥጋ ነው ብሉት
ደግሞም ደሜ ነውጠጡት
2
በቅዳሴ ጊዚያት
ይቀደሳል በሱ ስም
ያን ጊዜና ሰርክ እለት
ይታዘዛል ለቄስም ።
3
ሳይተው ሰማይንም
ከመንበር ላይ ይኖራል
እዚሁም ይቀመጣል
ደስ እንዲለው ወዱአል ።
4
እንጀራና ወይን የለም
ያምላክ ሥጋ ነው በውነት
እንጀራ ሆነ ሥጋም
ወይኑም ደም ሆነ በውነት።
5
መልኩ ነው የሚቀረው
ስእሉና ጣሙ ሽታው
በዚሁም በንጀራው
አሉ ደሙና ሥጋው ።
6
ይህን ምሥጢር እንመን
እናመስግነው እሱን
ዓይናችን ቢሳሳት
ያስረዳናል ሃይማኖት
17. እነሆ የዋህ በግ
እነሆ የዋህ በግ
እውነተኛው መስዋእት
የታረደልን ለህግ
ኑ እንስገድለት
1
የዋህ አባታችን
መልካም እረኛችን
በውነት ወዳጃችን
መድኃኒታችን ።
2
የኛ አምላክ የኛ ንጉሥ
በውነት አንተ የሱስ
ምግብ ለኛ ነፍስ
ስንቆርብም ስንቀድስ ።
3
ሥጋና ደምህን
በውነት ሰጠኸን
የሕይወት ምንጫችን
ምግብ ለነፍሳችን ።
4
የነፍሴ ቃልኪዳን
እንዳልረሳህ አንተን
ጻፍልኝ መዝገብህን
በልቤም ጸጋህን ።
5
ለሰማይ ለምድር
የሚያስጨንቅ ምሥጢር
ይኖራል በመንበር
ልንበላው ዘወትር
6
የፍቅር እሳት
የሕይወት መብራት
በዚያች ቀን ሰዓት
ነፍሴን አድናት ።
18. ላንተ እንስገድ መስቀል ሆይ
የክርስቶስ ሕማማት
ላንተ እንስገድ መስቀል ሆይ
የሱስ አለ አንተ ላይ ᎓᎓
1
ላንተ እንስገድ መስቀል ሆይ
ጨንቆት አልጋው ጌታችን
እንሳለም አንተን ቀርበን
ባንተ ሆኖ ተቤዠን ።
2
ላንተ እንስገድ መስቀል ሆይ
ክብር የሌለው እንጨት ነበርህ
ጌታ ክርስቶስ ተሰቅሎብህ
ለኛ ሁሉ መጠጊያ መጠጊያ ሆንህ ።ለኛ ሁሉ መጠጊያ መጠጊያ ሆንህ ።
3
ላንተ እንስገድ መስቀል · ሆይ
የጌታ ደም ቀደሰህ
እንባው ደግሞ አራሰህ
ካምላክ ጋራ እኛን አስታረቅህ ።
4
ላንተ እንስገድ መስቀል ሆይ
ጌታ አረገህ እጮኛው
ክንዱን ባንተ ዘረጋው
ሰውን ሁሉ ሊያድነው።
5
ላንተ እንስገድ መስቀል ሆይ
የጐልጐታ ሥቃይህን
እንዳይረሳው ልባችን
ስበርልን ብርታቱን ።
6
ላንተ እንስገድ መስቀል ሆይ
ሞተን ካለም ስንለይ
በፍርድ ቀን እዚያ ላይ
አንተ አብራልን እንደ ጣይ ።
19. ክርስቲያኖች የመጣችሁ
ክርስቲያኖች የመጣችሁ
የክርስቶስን ሕማም ስሙ
ስለናንተ ክፋት ነውና
እንዲህ መታመሙ
በዚህ ሕማም በርትታችሁ
ለመሞታችሁ
ያምላክደም ሲፈስ አይታችሁ
አፍሱ ከንባችሁ
1
ባትክልቱ ብርቱ ጦርነት
ልቡ ይሰማል
ሲጨነቅ ልቡ ሲታወክ
ተስፋ ያደርጋል
አንድ ጊዜ በብዙ ፍራት
አንድ ጊዜ በመውደድ
በኋላ ፍቅር አሸነፈ
መሞትን ወደደ ።
2
ይሁዳ ክፉነቱን ይዞ
መጣ ወይ እፊቱ
በመሳም አሳለፈው
ለጨካኝ ጠላቱ
ኃጢአተኛም እንደዚሁ
ክፉ ያደርጋል
በውሸት ኢየሱስን
እንዲያየው ይቀርባል ።
3
በተናቀ ወታደር እጅ
አለፈ አሁን
የሚያስፈራ ግርማውን
ነኩት ወይ ፊቱን
ለመላእክት በዚያን ጊዜ
ክርስቶስን ማስከበር
የክፉዎችን ለመቆጣት
ይገባ ነበር ።
4
ወደ ሊቀ ካህናቶች
ይዘው ወሰዱት
ክርስቶስን አላምንም አሉ
ሰደበ በማለት
በፍርዱ ቀን ተራውን
መድኃኔ ዓለምም
ሊቀ ካህን ያምላክን ፍርድ
ሳያሳይህ አትቀርም ።
5
በፈቃዱ የሱስ ክርስቶስ
ሲሰዋ ራሱን
ደኅና ሰው ተስማማበት
ሲበድል እሱን
ጴጥሮስ እንኳ እረስቶት
እንግዳ አለው
የሱስ ግን ባይኖቹጮራ
እንዲያዝን ወጋው ።
6
እጲላጦስ እሹሙ ፊት
ከክፉ ቈጠሩት
ከመጥፎ ሕዝብ የምሰማው
በርባንን ተዉት
እንዴት ያለ አመራረጥ
ክፉ ማፍቀር
ንጹሕን ይጥፋ ብለው
ክፉው ይቅር ።
7
ልብሱን ገፈው ያስሩታል
ባንድነት መክረዋል
በበትር ሲወድቅ አያለሁ
ጥሩ በግ ይመታል
ይህ ግፍ ለኛ ይገባ ነበር
አታንገላቱት
ሊያጥብ ነው የፈሠሠው ደም
የላንተን ክፋት
8
የሾህ አክሊል ወጋው
ግምባሩን
መዳኛችንን
ያለም ሰው መልካም ገዢውን
ማሳፈር ለምን
ክርስቶስ ተጨንቆላችሁ
እያያችሁ
እናንተ ደስ ብሎ አችሁ
ታጌጣላችሁ ።
9
ቀራንዮ ይሔዳል አዝግሞ
ግንድ ተሸክሞ
ቃል ያሰማል እንደ መምር
ሆኖ
እዚያ ቦታ ቆሞ
አባቴ ሆይ ይቅር · በላቸው
የበደሉኝን
እንዲህ ማድረግ ይገባል አሁን
ለክርስቲያን ።
10
ብዙ ሰዎች እያንገላቱት
እያሉ እየ ሰደቡት
ከጭንቁ ሲያመልጥ እንየው
እንድናምንበት
ከችንካር ባለ መቸገር
ያመልጥ ነበር
ያስቸገረው በብርቱ ማሠር
የናንተ ፍቅር ።
11
ጌታዬ ሆይ አደራ አትውረድ
ከሕማም አልጋህ
የኃይልህን ሥልጣን ከልክለህ
እስከ መሞትህ
ቀድሞ ተሥፋ የሰጠኸንን
ፈጽምልን
በፍቅርህ ከአንተ ጋር እንሙት
ወደ አንተ ሳበን ።
12
ነፍሱን ሰጠ አዘነ ፍጥረት
በፈጣሪ ሞት።
ያላዘነ አንድ እንኳን የለም
ከፍጡር ዓይነት
ልቤ ጭንቁን መሞቱን ሲያይ
አያዝንሞይ
ከጠንካራ ከደንጊያ ይልቅ
ይበረታል ወይ
20. እኔ ክርስቲያን ሆንሁ
እኔ ክርስቲያን ሆንሁ
ክርስቶስን ተከተልሁ
ክርስትና የተነሣ
ነፍሱ ዳነች ከወቀሳ ።
1
እኔ ክርስቲያን ሆንሁ
በመስቀሉ ተማጠንሁ
ክርስቶስን ቢከተሉ
በደሥታ ይኖራሉ ።
2
እኔ ክርስቲያን ሆንሁ
ካምላክ ጸጋ አገኘሁ
ለዘላለም ወደደኝ
ከመላእክቶች ቈጠረኝ ።
3
እኔ ክርስቲያን ሆንሁ
አዲስ ፍጥረት ተሠራሁ
የአምላክ ቄስ የቀባኝ
ነፍሴን ንጹሕ አረገኝ ።
4
እኔ ክርስቲያን ሆንሁ
በምሳሌውእኔ ተፈጠርሁ
በኃጢአት አጥፍቼው
በምሕረቱ መለሰው ።
5
እኔ ክርስቲያን ሆንሁ
በመከራው ተወጋሁን
እሱ አሳየን · ጭንቀቱን
ከኋላ ጭንቅ ሊያድነን ።
6
እኔ ክርስቲያን ሆንሁ
በጠባዬ ከርሱ ራቅሁ
ጌታ ቢሆን ሳይከፋ
ጠብቆናል እንዳንጠፋ ።
7
እኔ ክርስቲያን ሆንሁ
ከገነቱ እንኳን ሔድሁ
መሰደዴን አየውና
መጥቶ አዳነኝ ራራና ።
8
እኔ ክርስቲያን ሆንሁ
በየሱስ እጅ ተጠበቅሁ
የሰው ሥራ ከንቱ ነው
ቸሩ ልብህ ይማረው ።
9
እኔ ክርስቲያን ሆንሁ
ከችሮታህ ተመገብሁ
የኛን ክፋት ተወውና
አባቶችን እርዳ ናና ።
10
እኔ ክርስቲያን ሆንሁ
ማርያምን እርጂኝ አልሁ
የኛ ጌታ እናት ነሽ
አይጥናብን ገር ልብሽ ።
11
እኔ ክርስቲያን ሆንሁ
ሚካኤልን አከበርሁ
ዲያብሎስን አሸነፈ
ለኛ እርዳታ መች አረፈ።
12
እኔ ክርስቲያን ሆንሁ
ልመናዬን አቀረብሁ
በፍርድህ ቀን እንዳንቀር
ክፈትልን ያንተን በር ።
21. ፋሲካ ተነሣላችሁ ደስ ይበላችሁ
1
ተነሳላችሁ ደስ ይበላችሁ
ከእግዜርም ጋራ
አስታረቃችሁ
ሰብሮ መቃብሩን ተነሳልን
የክብር ንጉሥ ተነሣ ኢየሱስ
2
ሽቱዋን ይዛ ለመቃብሩ
ገና ሳይመጡ ደቀ መዝሙሩ
ደረሰች በፊት መግደላዊት
ብትመለከት ማንም የለበት ።
3
ጥዋት በማለዳ ገና ሳይነጋ
ጴጥሮስ ዮሐንስ ተነሱ አንድጋ
ሊያይ ገባ ጴጥሮስ ወደ መቃብር
ትንሣኤን አመነ ሳይጠራጠር ።
4
መቃብሩንም ሲያዩ በጣም
ታያቸው መልአክ ለብሶ ብርሃንም
ጌታ ተነስቷል እዚህ የለም
ገሊላ ሄዷል ተናግሯል ቀድሞም ።
5
ደቀ መዛሙርቱ ማታ በውድቅት
ተሰብስበው ሳሉ ሁሉ ባንድነት
ጌታ መጣላቸው እመሀላቸው
እንዴት ደስ ይላቸው ሰላም ሲላቸው
6
ቶማስ ቢጠራጠር በትንሣኤው
የሱስ ተገለጠ ሊያሳምነው
አትጠራጠር ቁስሌን ና እየው
እኔ ነኝ እመን ጥርጣሬን ተው ።
7
ዲዲሞስ አመነ ስላየ ቁስሉን
የችንካሩን ቦታ የእግሩና የእጁን
ወድቆም እመሬት ሰገደለት
አምላኬ ጌታዬ አንተ ነህ በውነት
8
እሰይ ተነሣልን ደስ ይበለን
ስብሐት ለማርያም ልጅ ድል ለነሣልን
ይክበር ይመስገን ለዘላለም
በውነት እርሱ ∶ ነው መድኃኒዓለም ።
22. አስርቱ ቃላት
ለኢየሱስ ክብር ክብር ለማርያም
ይገባቸዋል ለዘለዓለም
1
ላንድ አምላክ ብቻ ስገድ
ከርሱ በቀር አትውደዱ
ስሙንም በጣም አክሩ
በከንቱም እርሱን አትጥሩ ።
2
ሰንበት ቀንንም አክብሩ
በአሳብ እግዜርን አኑሩ
አባት እናትን አክብሩ
በቡራኬአቸውም ኑሩ ።
3
በአሳብ ሰውን አትግደል
በሌላውም አትበድል
ወደ ምንዝርም አትሂድ
ክፉ ነገርም አትውደድ ።
4
የሰውን ገንዘብ አትስረቅ
በክፋትም አትደብቅ
እግዚአብሔርን ወደህ አጥብቅ
ከሀሰትም እንድትርቅ ።
5
የታዘዘን በዓል አክብር
ኃጢአትንም ፈርተኸው ኑር
እሁድንም በዓልንም
መጥተህ ስማ ቅዳሴንም ።
6
ኃጢአትንም በሰራኸው
በየዓመቱ ተናዘዘው
በፋሲካ በበዓል
ቍርባንን ተቀበል ።
7
የጌታ ጾም ሊመጣልህ
ፈርተህ እራቅ ከኃጢአትህ
አርብንና ቅዳሜን
ስጋ አትብላ ሁለቱን ።
23. ቅዱስ ኢያቄም
ፍቅር ክብር ለኢያቄም
ያለም ሁሉ መድኃኒት
ተገኝታለች ከርሱ ቤት
ይገባዋል ዘለዓለም ።
1
ፍቅር ክብር ለኢያቄም
መልካም ዱር ነው የሱ ቤት
ደግ አንበሳ ወጣበት
ስለ ሕዝቡ የሚሞት ።
2
ፍቅር ክብር ለኢያቄም
የኢያቄም አንበሳ
በመስቀል ላይ ቢያገሳ
ሰይጣን ጓዙን አነሳ ።
3
ፍቀር ክብር ለኢያቄም
ይሁን ሰይጣን እርጉም
አሳፈረው ኢያቄም
በልጁ በማርያም ።
4
ፍቅር ክብር ለኢያቄም
ይሁን ሰይጣን ክፉ ወርጅ
አሳፈረው የሱ ልጅ
ወስዶ ጣለው ሲዖል ደጅ
5
ፍቅር ክብር ለኢያቄም
ይህ ሰይጣን ምን ሽባ ነው
የኢያቄም ልጅ የሞተው
ሰይጣንን ታስሮ አሰረው ።
6
ፍቅር ክብር ለኢያቄም
ዘካርያስ አለቃው
ኢያቄም ልጅ ሲሰጠው
ምን ያህል ነው ደስታ ።
24. ቅዱስ ጴጥሮስ
ቅዱስ ጴጥሮስ ሊቀ ሐዋርያት
የሃይማኖትም መሰረት
አንተ ነህ በሩ ለገነት
እንዳትረሳን የዚያን ዕለት
1
እረኛ ሆነህ አሰምሪያችን
እንዳይጠፋ ሃይማኖታችን
አንተን ሰጠን ክርስቶስ ጌታችን
እንድትረዳን እስከ ሞታችን ።
2
እንደራሴ ለክርስቶስ
ፈራጅ ቆራጭ አፈ ንጉሥ
አድርጎ ሾመህ ለሁሉ ነፍስ
እንዳንጠፋ በዲያብሎስ ።
3
መናፍቃን አንዳያጠፋት
ካቶሊካዊትን ሃይማኖት
ጠበቃ ነህ በአምላካችን ፊት
ስለዚህ አይነካንም ፍራት ።
4
የፈታኸው እንዲፈታ
ያሰርኸውም እንዳይፈታ
ስልጣን ሰጠህ ክርስቶስ ጌታ
አነገሰህ በሁሉ በታ ።
5
ሞትህ ሆነ በመስቀል ላይ
እራስህ በታች እግርህ በላይ
ግፍ ሰሩብህ ክፎች አንድ ላይ
እንዳንተ የለም ለጌታ አገልጋይ።
6
ባልንጀራህ ቅዱስ ጳውሎስ
ቢኣሳድዳችሁ በፈረስ
ደረሰበት ድንገት ኢየሱስ
ገለበጠው ልቡን በመንፈስ ።
7
ኢየሱስ ቢገለጥለት
ሊቀላቀል ከሐዋርያት
አስቀድሞ መጣ አንተ ቤት
ሊማከርኽ ደንቡን በስራት ።
8
አብሮ ሞተ ካንተ ጋራ
እሮማ ላይ በአሕዛብ ካራ
ሐይማኖትን በደሙ ዘራ
በቀለችም በሁሉ ስፍራ።
9
ኢየሱስን ያላመነ
ማርያምን ያላመነ
ለዲያብሎስ ለሰይጣን ሆነ
እሳት ገባ ቀረ ማከነ ።
25. ቅ እንድርያስ ።
ቅዱስ እንድርያስ
አንተ ነህ በፊት
ጌታ የመረጠህ
ሐዋርያነት
1
ቅዱስ እንድርያስ አሣ ስታፀምድ
ከወንድምህ ጋራ ከጴጥሮስ ጋራ ባንድ
ኢየሱስ ጠራችሁ በታላቅ መውደድ
ነፍሳትን ለማፅመድ እውቀት ሊያስለምድ ።
2
እናንተም በቶሎ ተከተላችሁ
የዓለምን ምኞት ሁሉን ትታችሁ
በኑሮአችሁ ሁሉ እሱን መስላችሁ
በምግባር በትምርት ብርሃን ሆናችሁ ።
3
በስራህ በፍጹም ጌታን መስለህ
የመስቀል መከራው ተካፋይ ሆነህ
ለየሱስ ክርስቶስ በውነት መስክረህ
እንድርያስ ሞትህ ወይ አግድሞ ተሰቅለህ
4
እውነተኛ ፍቅሩ በዚሁ ታውቋል
በሥራው በሞቱ ጌታውን መስሏል
አሁንም በክብሩ አብሮት ይኖራል
ኋላም በፍርድ ቀን አብሮ ይፈርዳል ።
5
ቅዱስ እንድርያስ ባልደረባህን
እርዳ በችግሩ አባታችንን
ለኛ ለበጎቹ የሚያስበውን
ተንኮለኛ ጠላት አውሬ እንዳይፈጀን ።
26. ቅዱስ ሚካኤል
ቅዱስ ሚካኤል ሆይ
በታላቅ ሀብትህ
ሲቸግረን ድረስ
አባታችን ነህ ።
1
ታላቅ መልአክ ሆይ አንተ ነህ በፊት
ያምላክን ትእዛዝ ቃሉን ለመስማት ።
መላእክት ጽልመት በግርህ ስር ወደቁ
ነያምላክን ትእዛዝ እንዳንተ ባይጠብቁ ።
2
ታላቅ መለአክ ሆይ በጦርነት ነን
አንተ እንደ ልማድህ ድል መንሣት ስጠን
አሎህን ተከፈል የልጆችህን
የቀድሞውን ጠላት እናጥፋው እርዳን ።
3
ቅዱስ ሚካኤል ለኛ እዘንልን
በሞታችን ጊዜ በክንፍህ ያዘን
ደክመንም እንዳንክድ ምክርህን ስጠን
ጥፋት እንዳይወስደን በክንፍህ ጋርደን ።
4
ትሁት መልአክ ሆይ ስደተኛን ነፍስ
በፍርድ ቀን ላምላክ የምትመልስ
በዚያ በፍርድ ቀን ጠበቃችን ሁን
የሰይጣንን ወገኖች ድል እንዳይነሱን ።
5
የእግዚአብሔር ምእመን ታላቅ መልአክ ሆይ
የሰማይን ተድላ አርገን ተካፋይ
ክርስቲያኖች ሁሉ ከትዛዝ ወጥተው
ለጥፋት ቀርበዋል እዘንላቸው ።
27. ቅዱስ ፈረንሲስኮስ
ና ቅዱስ ፈረንሲስኮስ
ስንሞት
ነፍሳችንን አንተ
አጥራት
1
ሙሉ አሳብህ ፈረሲስኮስ ሆይ
በተመስጦ ቢደርስ እሰማይ
ያለም ምኞት ወዳንተ ሳያይ
እንደ ክርስቶስ ኑሮህ ሆነ ወይ ።
2
እንደ ጌታ በረት ተወለደህ
መወለድህን አምላክ ወዶልህ
ከሰው በላይ አብልጦ ባርኮህ
በላይ በታች የለ እሚመስልህ ።
3
ማነው ከቶ እንዳንተ የተጋ
ጎልጎታን በማሰብ የሠጋ
ተከትሎ በየሱስ · ፍለጋ
ዕድሜ ሙሉ ሞቱን ያልዘነጋ።
4
ብሩሁ ችንካር ልብህን ቢጨንቀው
በግርህ በእጅህ ቁስሉን ዓተመው
ምኞትህንም አብረህ ሰቀልኸው
አዲት ደቂቅ መች ተለየኸው
5
የኛ አባት ሆይ የክርስቶስ ሰው
ልባችንን እንዳንተ አራራው
መስቀሉን ቍስሉን ይውደደው
አታላዩን ዓለም አስጠላው ።
6
ጻድቁ ሆይ የሱራፌል ህብር
የኛን ጩኸት አቅርብ ለእግዚአብሔር
ያላመኑት አምነውት ይክበር
ከሰው ወገን አንድም እንዳይቀር ።
28. ቅዱሳን ሁሉ
የሰማይ ጻድቃኖች
የእግዚአብሔር ወዳጆች
በትዕግሥታችሁ
መንግሥት ወረሳችሁ ።
1
ብትታዘዙለት
ለፈጣሪአችሁ
የዓለምን እውከት
ድል አደረጋችሁ
2
ቅዱሳን መላእክት
በሰማይ ያላችሁ
ያምላካችሁን ፊት
ዘወትር ታያላችሁ
3
ለጻድቃኑ ጌታ
ሲሰጣቸው ቦታ
ምን ያህል ደስታ
እንዴት ያለ እልልታ ።
4
ስጋዊ ፍትወት
በምድር ያገኛቸው
ቅ ዮሴፍ ።
የሰማዩ ማኅበር ዮሴፍ ያከብርኻል
የምድር ላይ ማኅበር በማመስገን ይጋል
አሁን በሰማያት
እንዴት ደስ ይላቸው
5
ስለ መልካም ነገር
ሁሉንም ትተው
ባረካቸው እግዜር
ደመወዝ ሰጣቸው ።
29. ቅዱስ ዮሴፍ
የሰማዩ ማኅበር ዮሴፍ ያከብርኻል
የምድር ላይ ማኅበር በማመስገን ይጋል
የግዜርን ቤት ድንግል በጅግ ጥሩ በዓል
ወሰድኻት አንተ ልትሆን ባል ።
1
አምላክ ላደረገው ስለ ሰላማችን
በዚህ ላንተ ሐዘን መጣብህ
በዚያ ቀን መልአኩ ቢነግርህ
የእግዚአብሔር መሆኑን ደስ አለኽ ይህን ለማመን
2
ንጉሡ ቢከፋ ጌታችንን ይዘህ
ወደ ምስርአገር ተከትለኽ ሸሸኽ
በኢየሩስዓሌም ሽተኸው አገኘኽ
አልቅሰኽ ደግሞም ደስ አለኽ ።
3
ሰው ካልሞተ በቀር ገነትን አይወርስም
ሰው ካልሞተ በቀር እግዜርን አያይም
አንተ በምድር ሳለኽ ኖረኻል ካምላክም
ገነትን ሆናለች ቤትኽም ።
4
ቅዱስ ዮሴፍ ሆይ እጅግ ንጹሕ ጌታ
እግዜርን ወደድኸው እኛንም አበርታ
ፈልገንህ እንሂድ አገራችን ይበርታ
እንድናገኝም ደስታ ።
5
እጅግ ደግ የኛ አምላክ ዮሴፍ ያሳደዝህ
ጸሎትን ተቀበል ዜማችንንም ባርክ
ስለ ዮሴፍ ስም እኛንም ቶሎ ማርክ
ኋላም ባንተ እንባረክ ።
30. ቅዱስ ዮሴፍ ሆይ ጠብቀን
ቅዱስ ዮሴፍ ሆይ ጠብቀን
ወደ ገነትም አድርሰን ።
1
የማርያም እጮኛ ሆይ
ቅዱስ ዮሴፍ ሆይ
ጠብቀህ ያምላክን ልጅ
ለኛም ሁን አማላጅ
2
እግዜር ከሴቶች ሁሉ
ባረከ ማርያምን
ደግሞም ከወንዶች ሁሉ
ባረከ ዮሴፍን ።
3
የፈጠረ ሁሉን
ቢወለድ በበረት
አንተ አባት ብትሆን
አገባኸው እቤት።
4
በሰማይ በላይኛው
አንድ ጌታ የሌለው
አንተ ብታሳድገው
ታዘዘልህ ላንተው ።
5
እመቤታችን ሊጣኒያ ።
ሔሮድስ ቢፈልገው
እገላለሁ ብሎ
ምድረ ግብጽ ወሰደው
አድናለሁ ብሎ ።
6
ስለ ደረሰ እድሜህ
ያዳም ሞት መጣብህ
ቡራኬን ከልጅህ
ተቀብለህ ሄድህ
7
እጅግ ክቡር ዮሴፍ ሆይ
ሲፈረድ በምድር ላይ
ለነፍሳችን እዘን
ተስፋ አርገናል አንተን።
8
ክርስቶስን እንዲአውቀው
ላማረው ሁሉ
እውነት ሃይማኖት ሰጠው
ክብር አንተ በሁሉ ።
31. እመቤታችን ሊጣኒያ
ድንግል ማርያም ለምኝልን ።
1
ንጽሕት እመቤት
የእግዚአብሔር እናት
የኢየሱስ እናት
የእግዚአብሔር በግዕት
ልክ የሌለሽ ንግሥት
የእስራኤል ምኞት
እጅግ ውዲት ንግሥት
ብርሃነ ገነት ።
2
እጅግ ውብ እመቤት
የክርስቶስ እናት
አንቺ ጥሩ ፍጥረት
የእግዜር ቃል እናት
እውነተኛ አብነት
የምሥጢር ገነት
የተመረጥሽ ሐብት
የሰላም ንግሥት ።
3
እጅግ ጠባብ እናት
ሁኝን እረዳት
የታመንሽ አዛኝት
ደግፊን በውነት
የጋልሽ እሳት
ኮከብ ንጋት
መልካም ሽቱ እመቤት
የክብር አታክልት።
4
የጻድቅ መሥተዋት
የንጉሥ ወርቅ ቤት
የምስጢራት ታቦት
ጹንዕት ሃይማኖት
በውነት ቅጥይ እናት
አንቺ በትረ መንግሥት
ግሩም ታምራት
ላወቀሽ ፍጥረት ።
5
እጅግ ጥሩ ንግሥት
የአሮን ታቦት
የገሊላ ተፍስሕት
መልካም አታክልት
የዋህ ንጽሕት እናት
አድኝን በውነት
አንቺ ሙሉ እመቤት
የሽቱ አታክልት ።
6
ንግሥት መላእክት
የክርስቲያን ረዳት
ላንቺ ይሁን ስብሐት
የምእመናን ሐብት
የመቁጠሪያ ንግሥት
የማት ፈርስ ቤት
ስሚን የኛን ጸሎት
የሰማይ ትርሲት ።
7
የጥበብ መስታየት
አንቺ ጽዋ ስብሐት
የሕይወት ምክንያት
የክርስቲያን መብራት
ተስፋ ሁኝን ንግሥት
አድኝን በውነት
የሁሉ መድኃኒት
ምሪን እገነት
32. ክብር ላንቺ ለሰማይ እመቤት
ክብር ላንቺ ለሰማይ እመቤት
ለኪ ሰላም ፍቅርና ስብሃት
የአዳም ተስፋ ሁላችን እናት
ልባችንን ሰጠንሽ ሰጠንሽ ንግሥት።
1
እርገት ድንግል ተንስአት በኣማን
ተቀመጠች ከልጇ የማን
ዘውድ ደፋች አገኘች መንግሥትን
ተዘጋጅቶ የጠበቃትን ።
2
ጌታም ደግሞ ሲሰጣት ሲሰጣት አክሊልን
ደስታዋ እንደ ምን ይሆን
መከራዋን በምድር በምድር ያገኛትን
ለወጠላት ልጅዋ በብርሃን ።
3
ቅዱሳንም ተቃጥለው በፍቅርሽ
ዋጋቸው ነሽ አንቺን ካገኙሽ
በደስታ ዙሪአሽን ከበውሽ
አንዲት ደቂቅ ምነው ባየሁሽ ።
4
እንግዴህስ እኔንም ጨምሪኝ
እንድሸለም አንቺን እንዳገኝ
ድንቁርና ድካም የከበበኝ
እንድወድሽ ብርሃን አሰጭኝ ።
5
ጽጌ ረዳ የገነት ነሽ መዓዛ
አዛኝ እናት የምርኮኞች ቤዛ
ያገራችን ፍቅርዋ ላንቺ እንዲበዛ
ብርሃን ስጫት ለጴጥሮስ ትገዛ
6
ቡርክት ዘር የሐና የኢያቄም
አለሽበት ላንቺ ይሁን ሰላም ይውረድ ለኛም
የፍቅርሽ ዝናም
እንድንበቅል እንድንለመልም ።
33. እላይኛው ሰማይ
እላይኛው ሰማይ
ሄጄ ማርያምን ልይ
1
ሄጄ ማርያምን ልይ
ወዳገሬ ገነት
እላይኛው ሰማይ
እርሷ እርሷ ናት ።
2
እርሷ እናቴ ናት
ተስፋዬም እሷ ናት
ደግሞም መድኃኒት ናት
ለዚህ ዓለም ሕይወት
3
እርሷ እናቴ ናት
የሁላችን ንግሥት
ልሂድ ወደርሷ ፊት
ፍቅሬን ለማሳየት ።
4
እርሷ እናቴ ናት
አሽከሯ ለመሆን
ላዚም ምስጋናዋን
ልምሰል መላእክትን
5
እርሷ እናቴ ናት
መሄድ እወዳለሁ
ወንበሯን አያለሁ
እኔም አከብራለሁ ።
6
እርሷ እናቴ ናት
እተዋለሁ ምድርን
እጠጋለሁ አንቺን
እንዳገኝ ፍቅርሽን።
34. ስላም ስላም ሰላም ለኪ
ሰላም ሰላም ሰላም ለኪ
ሰላም ሰላም ሰላም ለኪ ።
1
ከመለአኩ ጋራ
እጅ እንነሳለን
ከገብርኤል ጋራ
እንሰግድሻለን ።
2
ስምሽን ለማሞገስ
አፋችን አጣው
ዜማሽን ለማድረስ
እውቀት አቃተው ።
3
ገና ሳተጸነሽ
እግዜር አይቶሻል
ገና ርቀሽ ሳለሽ
እግዜር አውቆሻል ።
4
በላይኛው ሰማይ
አንቺ ባለሽ
ደግሞም በምድርም ላይ
አንችው አማርሽ ።
5
ውጋጋኑ ቢታይ
ንጊውም መጣ
አንቺ ብቅ ብትይ
ተስፋችን መጣ ።
6
ነግህ ኮከብ ወጣ
ምድሩበራልን
ፊትሽም በወጣ
እጅግ ደስ አለን ።
7
ከፋፋቴ ወሀ
አንቺ ጥሩ ነሽ
ከማር ከሌላውም
አንቺ ጣፋጭ ነሽ።
8
የሞትን መንገድ
ሔዋን ከፈተች
የሕይወትን መንገድ
ማርያም ከፈተች ።
9
የሰማይ ንግሥት
ለኛ እግዜርን
ትልቅ በረከት
አንቺ ለምኝልን ።
10
ኦ ክርስቶስ ኢየሱስ
ለጥሩ ደኃህ
ቡራኬን አፍስ
በአንተና በእናትህ ።
35. የእመቤታችን ዜማ
1
ከመለአኩ ጋራ
እጅ እንነሳለን
ከገብርኤል ጋራ
እንሰግድሻለን ።
2
ስምሽን ለማሞገስ
አፋችን አጣው
ዜማሽን ለማድረስ
እውቀት አቃተው ።
3
ገና ሳተጸነሽ
እግዜር አይቶሻል
ገና ርቀሽ ሳለሽ
እግዜር አውቆሻል ።
4
በላይኛው ሰማይ
አንቺ ባለሽ
ደግሞም በምድርም ላይ
አንችው አማርሽ ።
5
ውጋጋኑ ቢታይ
ንጊውም መጣ
አንቺ ብቅ ብትይ
ተስፋችን መጣ ።
6
ነግህ ኮከብ ወጣ
ምድሩበራልን
ፊትሽም በወጣ
እጅግ ደስ አለን ።
7
ከፋፋቴ ወሀ
አንቺ ጥሩ ነሽ
ከማር ከሌላውም
አንቺ ጣፋጭ ነሽ።
8
የሞትን መንገድ
ሔዋን ከፈተች
የሕይወትን መንገድ
ማርያም ከፈተች ።
9
የሰማይ ንግሥት
ለኛ እግዜርን
ትልቅ በረከት
አንቺ ለምኝልን ።
10
ኦ ክርስቶስ ኢየሱስ
ለጥሩ ደኃህ
ቡራኬን አፍስ
በአንተና በእናትህ ።
36. የደስታ ምስጢር አግኝተሻልና ሞገሥ
የደስታ ምስጢር ።
አግኝተሻልና ሞገሥ
ማርያም ደስ ይበልሽ ደስ
ደስ ይበልሽ ደስ ።
1
መለአኩ ማርያም
ወርዶ ከፊትሽ ሲቆም
ምን ይመስል ምን ይገርም
ሰላም ለኪ ማርያም ።
2
ምን የታደለች ፍጥረት
ያቺ የዮሐንስ እናት
ለመጐብኘት ሄደሽላት
ሶስት ወር ሙሉ እርሷው ቤት።
3
ኢየሱስን ትጸንሻለሽ
ትወልጃለሽም ሲልሽ
ምን ያህል ደስታሽ
የማክበሩስ ድንጋጤሽ ።
4
ተወልዶ ባርባው ዕለት
ቤተ መቅደስ ወሰዱት
ስምኦን በእጆቹ አቅፎት
አቀረበው ለመስዋዕት።
5
በአስራ ሁለት አመቱ
ቤተ መቅደስ በመቅረቱ
አዝና ነበረች እናቱ
ደስም አላት መገኘቱ።
37. ለበደለ ስሙ ባልደረባ
የሐዘን ምስጢር ።
ለበደለው ሰው ባልደረባ
አንቺ ነሽ ጽጌ ረዳ አበባ
ጽጌ ረዳ አበባ
1
ሐሙስ ማታ በውድቅት
ተለይቶ ከአርድእት
ጸሎት ሲያደርግ በአትክልት
ደም ሆነ ወዙ ቅጽበት ።
2
ባደባባይ እንደ ወርፍ
ተፈርዶበት በሹም አፍ
ቢያስገርፉት በዥራፍ
ደሙ ፈሰሰ እንደ ጐርፍ።
3
አይሁድ ሲቀልዱበት
የሾህ አክሊል ደፉበት
መቃ በጁ አስጨበጡት
ከለሜዳም አለበሱት ።
4
ፈርደውበት እንዲሞት
የግፋቸውም ብዛት
መስቀሉን አሸከሙት
መከራውን ለማብዛት
5
ሲጨርስ ተራራውን
ቸነከሩት እግር እጁን
ጌታችን አምላካችን
እኛ ነን እንጂ ።
38. የስማይ የምድር እመቤት
የክብር ምስጢር ። ።
የሰማይ የምድር እመቤት
ልጅሽ ተነሣልሽ ከሞት
ተነሣ · ከሞት ።
1
ክርስቶስ በሦስተኛው ቀን
ተነሣልን ከሙታን
በታላቅ ኃይል በስልጣን
ማረካቸው ጻድቃን ።
2
በተነሣ ባርባ · ቀኑ
ዓይናቸውን እያቀኑ
ሲያዩት ወጣ እዙፋኑ
ቦታ ሊሰጥ ለጻድቃኑ ።
3
ደቀ መዛሙርቱ ሁሉ
ጽርሐ ፅዮን ባንድ ሳሉ
ጰራቅሊጦስን በሙሉ
ላከላቸው በአብ ቃሉ።
4
የሚወዳት እናቱን
አልተዋትም ጭራሹን
ልኮ መላእክቶቹን
ጠራት እፊቱ እንድትሆን
5
በልጅሽ ቀኝ ተቀምጠሽ
ጻድቃን ሁሉ ከበውሽ
የብርሃን አክሊል ደፍተሽ
ድረሽልን ስንጠራሽ ።
39. እጅግ ውድ እመቤት
እጅግ ውድ እመቤት
አንድ ዕለት
ልቀመጥ አንቺ ቤት
እገነት ።
1
ወደሽኛል አንቺ ውድ እመቤት
ያንቺ ፍቅር ልቤን አናወጣት
ያንቺ ሃሳብ ሕይወቴን አደላት
በምድርም ላይ ደስ ያሰኛል በውነት።
2
መች አያለሁ እመቤት ፊትሽን
ናፍቄአለሁ እኔም ያንን ቀን
እንዳይርቅም ከልቤ ሐዘን
እወዳለሁ ለማዜም ስምሽን ።
3
መንገደኛ ሲያስብ አገሩን
ይበረታል ሰርክ ዕለት በጣሙን
ያንቺ ፍቅር ይልቅ ወጋ ልቤን
ደግሞም አንቺ የኛን ተቀበይን።
4
በመከራ ነፍሴ ስትጨነቅ
ውድ ስምሽ መከራዋን ያርቅ
ሲለምኑ ያንቺን ክቡር ስም
ይሰጠናል ቡራኬ ሰማይም ።
5
ለሚጠራው ስምሽ ይጣፍጣል
እኔ ደግሞ ጠራሁሽ ሰርክለት
አውቃለሁ አንቺ ክብርት ድንግል
በፍቅርም አይተሽኛል በውነት።
40. ሰላም ማርያም
ሰላም ማርያም
እገነት እስክንሄድ
ምሪን መንገድ
ሰላም ማርያም ።
1
በላይኛው ሰማይ
የእግዚአብሔር መላእክት
አከበሩሽ በውነት
ንግሥት እመቤት ሆይ ።
2
እኛም በምድር ያለን
ልጆችሽ የሆንን
ክብርት እናታችን
ተቀበይን ዜማን ።
3
ከሰይጣናት ተንኰል
ከሰዎችም ክፋት
አንቺ ስጭን ብርታት
እንድናደርግ ድል ።
4
እርኩሳን መናፍሳት
አሰቡን ለጥፋት
አንቺ ንግሥታችን
ከክፉ ሰውሪን ።
5
ሊሞት የቀረበን
ተስፋውን አጥኝለት
ተቀብለሽ ነፍሱን
አግቢው ወደ ገነት
6
ያላመኑት ሁሉ
ይመኑ ኢየሱስን
ግራም ቀኝም ያለ
ይፈልጉት እሱን
41. ሰላም ላንቺ ምህረታዊት እናት
ሰላም ላንቺ ምህረታዊ እናት
ያምላክ እናት የይቅርታም እናት
የተስፋና የጸጋችን እናት
ቅድስትና የመላብሽ እናት
ኦ ማርያም ።
1
ሰላም ላንቺ ያዳም ልጆች ክብር
ሰላም ድንግል ከሁሉ ነሽ እጽር
በሰማይ ላይ የጻድቃኖች መንበር
የተቀመጥሽ ባምላክ ዙፋን እግር
ኦ ማርያም ።
2
ሰላም ፍጹም ድንግላዊ
የወለድሽው የኛ መድኃኒት
የሚገዛ ዓለም ሰማያት
የጸነሽው አምላክ ሰውነት
ኦ ማርያም ።
3
እናት የዘለዓለም አብ አንቺን ፈጠረሽ
አንድ ልጅም በኃይሉ ጸለለሽ
መንፈስ ቅዱስ በፍጹም ቀደሰሽ
ያምላክንም መሉ ዕውቀት ወረስሽ
ኦ ማርያም ።
4
በታምራት ፈጠረሽ አምላክሽ
አይኖቹንም ባንቺ ላይ ጣለብሽ
ሙሽራውን ለራሱ አደረገሽ
ከፍጡራን አብልጦ ወደደሽ
አ ማርያም ።
5
በዚህ ዓለም ትዛዝሽን ጠብቀን
በሰይጣን ላይ ድል አስነስተሽን
በበደልነው ከልጅሽ ከልጅሽ አስታርቂን
ካንቺም ጋራ በደስታ አኑሪን ማርያም ።
42. ሁኚ ለኛ ቤዛ
ሁኚ ለኛ ቤዛ
የተደነቅሽ ትንሽ ቴሬዛ
ሁኚ ለኛ ቤዛ
በዚህ ዓለም ችግር ሲበዛ
1
ልጅ ሆነሽ በሕፃንነትሽ
ሰማይን በመመልከት
የስምሽን ታላቅ ምልክት
አገኘሽ በከዋከብት
2
በደዌ በጥኑ ታመሽ
ቢጠና ይህ በሽታሽ
ለንግሥት አደራ አሉሽ
ተሳሉ እህቶችሽ ።
3
እርሱዋም በጣም ደስ ብሏት
ላንቺ ሳቀች በውነት
ያንቺም ድነሽ መጫወት
ድንቅ ነው ትልቅ ታምራት ።
4
ኑሮሽን እንደ ኤሊያስ
አደረግሽ በቃርሜሎስ
ብርታትሽ እየሆነ አዲስ
በማድነቅ አላቸው ደስ
5
እንግዴህ ምን ቀረሽ ይሆን
ካሸነፍሽ ከንቱ ዓለምን
ጽጌረዳ አበባ ሁኝን
የካርሜል አበባችን ።
6
ከፍቅርሽ ካበባው ቅንጣት
በትኚልን ጥቂት
ይበርታ ይጥና ኃይማኖት
አድኝን ካጉል ጥፋት ።
43. ቅድስት እናት ለዘላለም
ቅድስት እናት ለዘላለም
በልቤ ውስጥ እንዲታተም
የልጅሽ የሱስ ሕማም ።
1
ያዘን እናት የንባ ባሕር
ቁማ ነበር እመስቀል ስር
ተቸንክራ በፍቅር ።
2
ክቡድ ሐዘን የተጫናት
ነፍሷን ቦታ የጠበባት
የሐዘን ሰይፍ የወጋት ።
3
ዋ የጭንቅሽ የንባሽ ባሕር
መጠን የለው ስፍር ቁጥር
ቅድስት ያንድ አምላክ መንበር
4
ምን ይመስል ሐዘንሽ
ከመስቀሉ ያ ልጅሽ
ቁልቁል አንቺን ሲያይሽ
5
ማነው ከኛ እርሷን አይቶ
ያንን ጭንቋን ተመልክቶ
እንባ እማይወጣው ከቶ
6
ማነው ከኛ ሳያዝንላት
ደፍሮ ጭንቋን የሚያይላት
ለዚያች ላንድ አምላክ እናት
7
ስለ ሕዝቡ ኃጢአት
ኢየሱስን ሲገርፉት
ታየው ነበር ማየት ።
8
ያንን ልጅዋን ወዳጅዋን
እመስቀል ላይ ላይ ድካሙን
ታየው ነበር ሞቱን ።
9
ካንቺ ጋራ እንዳነባ
ያንቺ ሐዘን ልቤ ይግባ
ቅድስት የፍቅር አበባ ።
10
ልቤ እንደ እሳት እንዲ ቃጠል
ኢየሱስን በማገልገል
አማልጅኝ ቅድስት ድንግል
11
ያ አንዱ ልጅሽ · የሞተልኝ
ያለ መጠን የወደደኝ
ሕማሙ ሕማም ይሁንልኝ።
12
ላልቅስ ሳልቅስ ካንቺ ጋራ
ነፍሴ እስካለች ሳላባራ
ስለ ክርስቶስ መከራ
13
እመስቀል ስር በተገኘኁ
ካንቺ ጋራ ዋይ በነበርሁ
በደም እንባ በታጠብሁ
14
ከደናግል ሁሉ ድንግል
እንባ ይወጣል ስላንቺ ስል
ስለ ልጅሽ መስቀል
15
ሸክሜ ይሁን ያምላክ ሞቱ
ደግሞ እርስቴ ሕማማቱ
ትዝታዬም ግርፋቱ ።
16
እኔን ይውጋኝ ቁስሉ
ስክር ያድርገን በመስቀሉ
ክቡር ደሙን በሁሉ ።
17
አበሳዬ ለዚያ ለሳት
አሳልፎ እንዳይሰጣት
ድንግል ነፍሴን ታደጊያት
18
ነፍሴ ከሥጋ ስትወጣ
ኢየሱስ ሆይ ደጉን ዕጣ
ስለ እናትህ እንዳታጣ ።
19
ስበሰብስ አፈር ስሆን
የነፍሴ እርስት ገነት ይሁን
ኢየሱስ አደራህን ።
44. የሰው ልብ አንዲት ሆና
1
የሰው ልብ አንዲት ሆና
ሐዘንዋ አልፋልና
ኤክሌዚያም ባንቺ አምና
ታቀርባለች ምሥጋና
ድንግል ማርያም ።
2
ለልጅዋ ስታነባ
ተነሣና ቢገባ
ደስታ በጣም ጠግባ
ፈነዳች እንዳበባ
ድንግል ማርያም ።
3
በሰማያት በራማ
ያከብሯታል በዜማ
እኛም ለሷ ግርማ
እናዚም አዲስ ዜማ
ድንግል ማርያም ።
4
የደናግል ንግሥት
ስሚ የኛን ጩኸት
እምላኬ ሆይ ሞት ስትፈርድብኝ
በኋላ ስንሞት
አሰጪን ሽልማት
ድንግል ማርያም ።
5
ሥላሴ በአካላት
አንድ በመለኮት
ስለርስዋ ትሩፋት
አድርሰን ለሕይወት
ድንግል ማርያም ።
45. ለሙታን
አምላኬ ሆይ ሞት ስትፈርድብኝ
የመምጫውን ቀኑን ደበቅከኝ
በደግነት እንድኖር አርገኝ
የውነት ፍርድህ እንዳያስፈራኝ
ገሩ ኢየሱስ ።
1
የምታልፉት በዚህ አገደም
ኃብታሞችም ደግሞ ድሆችም
ከመቃብር እዩት የኔን ዐዕም
ለላንተውም ይኸ አይቀርም
ዋ ሰው ሆይ ።
2
በዚህ ደንጊያ የተጻፈውን
ቅረብና አንብበው ስሜን
ክፈትና ተመልከት ውስጡን
እሬሳዬ የመሰለውን
ዋ ሰው ሆይ ።
3
በውበቴ ባፍላ ልጅነቴ
ብዬ ነበር ብርቱ ነው ጕልበቴ
ድንገት ሆነ መውደቄና ሞቴ
አለሁ አትበል አንተም በሕይወቴ
ንስሓቸው ላልወረደላቸው
ዋ ሰው ሆይ ።
4
ሥጋ ተላ አፈር ሆነ ትሉ
የኛ ሥጋ አፈር ነው በሙሉ
ዐፅሞች እንኳ ልይትይት ይላሉ
ላዳም ያለው እግዜር ይህ ነው ቃሉ
ዋ ሰው ሆይ ።
5
እኔን አይተህ ለራስህ አስብ
የማይቀር ሞት ለሰው አደብ
ተከታይ ነህ በጣም አርገው ልብ
ተሰናድተህ ጠብቅ በጥበብ
ዋ ሰው ሆይ ።
46. ንስሓቸው ላልወረደላቸው
ክቡድ ሐዘን ለወደቀባቸው
መከራቸው ላላለቀላቸው
ያንቺ ምህረት ተስፋ ይሁናቸው
ኦ ማርያም ።
1
ምንጬ አንቺ ነሽ ለፍጹም ንጽህና
ሁሉን ንጹህ ታደርጊያለሽና
ዘርጊላቸው እጅሽን በጤና
ዕለት ዕለት ይጨነቃሉና
ኦ ማርያም ።
2
መሸሻቸው ወዳንቺ ብቻ እጅ ነው
ያውቃሉና እንድታድኛቸው
ፊትሽን አይተው መኖር ፈለጋቸው
ዘለዓለም ደስ ደስ እንዲላቸው
ኦ ማርያም ።
3
ባንቺ እጅ ነው ሰማይ መከፈቱ
ያላንቺማ ይጠፋል ፍጥረቱ
አይፈታም አላንቺ ሰንሰለቱ
አንቺ አውጫቸው ከታሰሩበቱ
ኦ ማርያም ።
4
የጻድቃን ህግ ጎዳና መሪያቸው
ለታመኑሽ በውነት ሕይወታቸው
ሙታንንም ዘውትር ጎብኛቸው
ከልጅሽም በጣም አማልጃቸው
ኦ ማርያም ።
5
እንባችንን የሚወርደውን
ተመልክተሽ አንቺ እናታችን
ነበልባሉን ይጥፋ በይልን
መኖረያቸው ሰማይ እንዲሆን
ኦ ማርያም ።
6
በፍርድ ቀን በሌለበት መድሎ
ሲፈራረድ ሁሉ ተጠቅሎ
ለኛ ድልን ለምኝልን ቶሎ
እንዲደርሰን እጣችን ተብሎ
ኦ ማርያም ።
47. አድምጡ እንበል ቀስ
አድምጡ እንበል ቀስ
ማነው የሚያለቅስ
ለማየት እንገስግስ
ቤተልሔም ድረስ ።
1
በፍቅሩ ሰው ቢወድ
እበረት ቢወለድ
ከዚያውም ማሳደድ
አየ ሰው አየ ጉድ ።
2
ሲዛ ሰማያት
ሲሰግዱለት መላእክት
ቢመጣ ከበረት
ማደሪያ ነፈጉት ።
3
ከአዋቂዎች ከካህኖች
ከጌቶች ከንጉሦች
ተሻሉ እረኞች
የነበሩት ከላሞች።
4
ተወልዶ እስከሞቱ
መከራው መብዛቱ
እያየች በጭንቀቱ
ምን ትገረም ያች እናቱ።
48. ሰማዮችም በላይ ያሉ
ሰማዮችም በላይ ያሉ
መሬቶችም ታች የዋሉ
በመደነቅ ዝም በሉ
አምላክ ሕፃን ሆነ አስተውሉ
አሸነፈ ፍቅር ጣለው ክብሩን ሁሉ
ግዛቱ ነው ምድር ሁሉ
መንግሥቱ ነው ዓለም ሁሉ
1
ምሳሌዎች የምታውቁ
እንደ ጥላ ሒዱ
ለውነት ቦታን ልቀቁ
አምላካችን ሰው ሆነ አድንቁ
የመጽሐፍ ቃሎች ትንቢቶች አለቁ
ግዛቱ ነው ምድር ሁሉ
መንግሥቱ ነው ዓለም ሁሉ ።
2
በጨለማ በኩለ ሌሊት
ለብቻዋ ድንግል እናት
ድንቅ ወለደች ያለም መብራት
በመገረም በዚች ሰዓት
ወንድማችን አልነው እሷንም እናት
ግዛቱ ነው ምድር ሁሉ
መንግሥቱ ነው ዓለም ሁሉ ።
3
በእልፍኝ በግርግም
ጋርደውታል እነላም
የብርድ ኃይል ተው ድከም
ፈጣሪህን አትጉዳ በጣም
አምላክ ሕፃን መሆን ድንቅ ነው ግሩም
ግዛቱ ነው ምድር ሁሉ
መንግሥቱ ነው ዓለም ሁሉ ።
4
ልደት ልደት ገና ገና
ፈጣሪያችን መጥቷልና
እስቲ እናዚም በምሥጋና
እውቀታችን አይበቃምና
ልባችንን ውሰድ ምርኮ አድርግና
ግዛቱ ነው ምድር ሁሉ
መንግሥቱ ነው ዓለም ሁሉ ።
49. ንጉሦች እንከተል
የንጉሦች ዜማ
ንጉሦች እንከተል
ይጓዛሉ ሰባ ሰገል
ንጉሦች እንከተል
በከዋከብት ተመርተዋል
1
ኮከቧ ብትመራን
ብንገባ ማንን አየን
ኮከቧ ብትመራን
አየነው ውቡን ሕፃን ።
2
ንጉሦች ከርሱ ሲማሩ
ግርግም ነው የሱ ወንበሩ
ንጉሦች ከርሱ ሲማሩ
ሕፃኑ ነው በችግሩ ።
3
የንጉሦች ንጉሥ ነውና
ስገዱ ንጉሦች ኑና
የንጉሦች ንጉሥ ነውና
በጥሩ አሳብ ልቦና ።
4
ወርቅ ዕጣን ከርቤም ቢሆን
አልፈቀደም እሱ ይህን
ወርቅ ዕጣን ከርቤም ቢሆን
የመረጠው ድህነትን ።
5
ንጉሦች ሲሰግዱለት
ዘውድ የለው በትረ መንግሥት
ንጉሦች ሲሰግዱለት
በረት ነው በድህነት ።
6
አንቺ ቦታ በጣም ታደልሽ
ለፈጣሪ አሥራት ወጣሽ
አንቺ ቦታ በጣም ታደልሽ
ንጉሦች ሰገዱብሽ ።
50. የሰማይ የምድር ንጉሥ
የሰማይ የምድር ንጉሥ
መንግሥትህ የማይፈርስ
አንተነህ ኢየሱስ ።
1
ያገረ ገዢዎች ራስ
የንጉሦች ንጉሥ
አንተነህ ኢየሱስ ።
2
ንጉሡ ነገሥታት
ላመኑት በሕይወት
ነህ ኢየሱስ ነህ በውነት ።
3
መንግሥትህ በጣም ይስፋ
የሰው ነፍስ እንዳይጠፋ
ክርስቶስየኛ ተስፋ።
4
በቁርባን ስውር ነህ
በሃይማኖት ላየህ
ኢየሱስ ሆይ ውብ ነህ
5
ስወድህ ውደደኝ
ስጠራህ ቅረበኝ
አላንተ ምን አለኝ ።
6
በፍቅርህ ተመርቼ
በሃይማኖት ጸንቼ
እንዳገኝህ በርትቼ ።
7
ያንተን ጣም ለቀመሰው
ትዝታህን ላወቀው
ሌላ ምንም አያምረው ።
8
ከፍቅርህ አልፋቅ
ከልብህ አልራቅ
አንተን ብቻ ልወቅ ᎓᎓
51. ና ፈጣሪ መንፈስ ቅዱስ
ና ፈጣሪ መንፈስ ቅዱስ
የምዕመናንህን ነፍሳት ጎብኝ
የላይኛውን ጸጋ ምላባቸው
አንተ በፈጠርኻቸው ልቦች።
1
ጰራቅሊጦስ የምትባል
የልዑል እግዜር በረከት
የሚቃጠል የፍቅርምንጭ
መንፈሳዊም ቅባት ።
2
፯ቱ ሀብታት አንተ ነህ
የአብ ቀኝ ጣቱ
አብ ተስፋ ላደረገልን መልክተኛ
የሰውን አፍ የምታበለጥግ።
3
ለነፍሳት ብርሃንህን አብራ
በልብም ፍቅርህን አፍስ
ከሥጋ ድካማችን ሁሉ
በኃይልህ ዘወትር አበርታን።
4
ጠላትን ከኛ አርቅልን
ቶሎ ዕርቅህን ስጠን
እንዲሁ አንተ መርተኸን
ከክፉ ሁሉ እንድንጠነቀቅ።
5
አብን እንድናውቅ አስተምረን
ወልድንም እንድናውቅ ኦስተምረን
አንተንም የሁለቱን መንፈስ
ዘወትርም እንድናምን።
6
፮ ስብሐት ለእግዚአብሔር አብ
ላንድ ልጁም ይሁን
ከመንፈስ ቅዱስ ጳራቅሊጦስ ጋር አሁንም ለዘለዓለምም ።
አሜን ።
52. ሰላም ማርያም ልባችን
ሰላም ማርያም ልባችንን ጠብቂልን
በሰማይ ቤት አንድ ቀን
ልጅሽን አይተን እንድንኖር።
1
በዛሬ ቀን ኦ ድንግል
ፍጹም ላንቺ ተሰጠን
2
ዓለም ከቦ ነፍሳችንን
ይፈትናል ሊነጥቀን ።
3
አገራችን ፍቅሯ ላንቺ
ፍጹም ይሁን ቅድስት ድንግል ።
4
በክንፍሽ ስር ተሸሽገን
እሰማይ ቤት እንድንደርስ
53. ግሩም ነው ድንቅ ነው የመቁጠርያ ወር
ግሩም ነው ድንቅ ነው
ያንቺ ወርኅ ጽጌ
ግሩም ነው ድንቅ ነው
ያንቺወርኅ ጽጌ ።
1
ጽጌሽ የኛ እመቤት ጥዑም መአዛ
ምሥጢሩም ድንቅ ነው የዓለም ቤዛ ።
2
ክብርሽን መተረክ ስፈልግ በጽጌ
ተሳነኝ አቃተኝ እንዴት አድርጌ ።
3
ከፍጡራን ጋራ ባለኝ ሕብረት
እንዲያው ሰላም ልበል እመቤት ።
4
አልችልም ብቻዬን ውዳሴሽን
ካልረዱኝ መላእክት ሰማዕት ጻድቃን ።
5
ድንቅ ነው ታሪክ የጽጌሽ ወር
አልደፍርም ላልችለው ባጭር ነገር ።
6
እንዲያው እልሻለሁ የልዑል መንበር
የኪዳን ታቦት ነሽ የጽጌ ሚስጢር ።